ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሐሙስ ኅዳር 17/2019 ዓ.ም. በተለያዩ ክልሎች የሚፈጸመውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ መፈናቀልና የፀጥታ መደፍረስ አንስተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጠይቀዋል። መንግሥታቸው ለችግሮቹ ምን እንደሚያደርግም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱ ፊት የቀረቡት በሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። በፖለቲካ፣ በፀጥታና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ከአባላቱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ነበር።
የኮሬ ማኅበረሰብ ጥያቄ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አወቀ ሃምዛዬ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግኝቶችን ጠቅሰው፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት አሁንም አስተማማኝ አለመሆኑን የገለጹት ዶ/ር አወቀ፣ በመንግሥት ኃይሎች፣ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች፣ በተለያዩ ቡድኖችና እሳቸው «ፀረ-ሰላም ኃይሎች» ባሏቸው ወገኖች ይፈጸማሉ የተባሉ ግድያዎችን፣ የአካል ማጉደልንና ዘረፋን አንስተዋል።
ችግሩ ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል የአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎችን፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋን፣ አርሲንና ሞያሌን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ሶዶንና አበሽጌን ዘርዝረዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት የኮሬና የቡርጂ ዞኖች ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ጋር የሚዋሰኑባቸውን አካባቢዎችም ጠቅሰዋል።
ዶ/ር አወቀ እንደገለጹት፣ የኮሬ ማኅበረሰብ «ጽንፈኛ ታጣቂዎች» ባሏቸው ወገኖች በተደጋጋሚ በሚፈጸምበት ጥቃት ምክንያት ላለፉት 11 ዓመታት የሕልውና ስጋት ተደቅኖበታል።
ለምክር ቤቱና ለፌደራል መንግሥቱ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢቀርብም ጥቃቱ አለመቆሙን ተናግረዋል። በቅርብ ቀናትም ሆነ እሳቸው ንግግር እያደረጉ ባሉበት ሰዓት ጥቃት መፈጸሙ መዘገቡንም ገልጸዋል።
«ይህ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነው የኮሬ ሕዝብ ለ11 ተከታታይ ዓመታት ያለማቋረጥ እየተወረረና እየተጨፈጨፈ ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ሳለ መንግሥት ጉዳዩን ለምን ቸል አለው? የዚህ ሕዝብ የወደፊት ተስፋና እጣ ፈንታስ ምንድን ነው?» ሲሉ ጠይቀዋል።
የአርሲ ተፈናቃዮች ጉዳይ
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባሉ አቶ ገብረመስቀል አደመ በበኩላቸው፣ መንግሥት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግር እየያዘ ያለበትን መንገድ ጥያቄ ውስጥ ከተዋል።
በአርሲ በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን ግድያና መፈናቀል ያነሱት አቶ ገብረመስቀል፣ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2026 በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ደርሷል ያሉትን «ዘግናኝ ጭፍጨፋ» እና መፈናቀል አስታውሰዋል። ተደጋጋሚ ጥቃቶቹ ነዋሪዎቹን ከለላና እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጓቸውም ተናግረዋል።
«በአካባቢው ያለውን የመንግሥታችሁን መዋቅር መፈተሽ አለባችሁ!» ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የመንግሥት ቅቡልነትና የሕዝብ አመኔታ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ፣ ድርጊቱን የፈጸሙትም ተጣርተው አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መንግሥት ምን እንደሚሠራ ጠይቀዋል።
ሌሎች ጥያቄዎችና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደዘገበው፣ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ከኤርትራ ጋር ስላለው ግንኙነት ጠይቀዋል። ኤርትራ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ትሰጣለች ያሉትን ድጋፍ በተመለከተ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነም ጠይቀዋል።
አባላቱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የታክስ ማሻሻያን፣ ሙስናን፣ የከተማ ልማትን፣ ግዙፍ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችንና ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነትም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ከጀርባው ዘላቂ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
«መከላከያ እንደ ቤት ነው። የመከላከያ ሠራዊቱን ብቻ ብንገነባ ዘላቂ አይሆንም። ኢኮኖሚው ሊሸከመው እንደሚችል ማረጋገጥ አለብን» ብለዋል።
ምክር ቤቱ የመንግሥትን አቋም ካዳመጠ በኋላ ወደ ድጋፍ ሞሽን ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።
