የአውሮፓ ኅብረትና ትሬድማርክ አፍሪካ ኅዳር 15/2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የ20 ሚሊዮን ዩሮ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲንና ሶማሊያን በሚያገናኙ የንግድ ኮሪደሮች ላይ ለአካባቢ ተስማሚ ትራንስፖርትን፣ ዲጂታል ንግድንና የአገራቱን ትስስር ለማሻሻል ያለመ ነው።
ስምምነቱ የተፈረመው የ2026ቱ የአፍሪካ ንግድና ልማት ፎረም ጎን ለጎን ነው። ለአራት ዓመታት የሚቆየውን መርሃ ግብር ወጪ የሚሸፍነው የአውሮፓ ኅብረት ሲሆን፣ ሥራው በአውሮፓውያኑ 2027 ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
መርሃ ግብሩን ተግባራዊ የሚያደርገው ትሬድማርክ አፍሪካ ከሦስቱ አገራት መንግሥታት ጋር በመቀናጀት ነው።
መርሃ ግብሩ የጭነት ትራንስፖርትን ለማዘመን፣ የዲጂታል ንግድ መሠረተ ልማትን ለማጠናከርና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ይሠራል። በተለይ ትኩረት የተሰጠው ለግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ሲሆን፣ ለእርሻ ምርቶች የሚስማማና ይበልጥ ቀልጣፋ የጭነት ትራንስፖርት ለማዘጋጀት ታቅዷል።
ኢትዮጵያ አብዛኛውን የውጭ ንግዷን የምታካሂደው በጂቡቲ ወደቦች በኩል በመሆኑ መርሃ ግብሩ ለአገሪቱ ትርጉም አለው። ኢትዮጵያን ከጂቡቲና ከሶማሊያ ጋር የሚያገናኙት ኮሪደሮች ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚላኩና ከዚያ የሚገቡ ዕቃዎች የሚጓጓዙባቸው መስመሮች ናቸው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ፣ መርሃ ግብሩ አገሪቱ የምታካሂደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በተለይም ንግድን የማቀላጠፍና የድንበር አስተዳደርን የማሻሻል ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
አጋርነቱ የኢትዮጵያን የገቢና የወጪ ንግድ እንደሚደግፍና አገሪቱን ከጂቡቲና ከሶማሊያ ጋር የሚያገናኙትን የንግድ ኮሪደሮች እንደሚያሻሽል ሚኒስትሯ ገልጸዋል። የቀጣናው የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሻሻል የኢትዮጵያ ምርቶች በአፍሪካ ቀንድና ከዚያም ባሻገር ወዳሉ ገበያዎች እንዲደርሱ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ፎረሙን ኢትዮጵያ እንደምታስተናግድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኅዳር 11/2019 ዓ.ም. አስታውቆ እንደነበር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፣ ፎረሙ የንግድ ሚኒስትሮችን፣ አህጉራዊ ተቋማትንና የንግዱ ማኅበረሰብ መሪዎችን በአንድ መድረክ ያሰባስባል። ተሳታፊዎቹ የተሻሉ የጥራት ደረጃዎችን በመጠቀም የአፍሪካን የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ይወያያሉ።
